በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 351 ተማሪዎችን አስመርቋል
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 351 ተማሪዎችን አስመርቋል።
___________________________________
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ በተካሄደ 4ኛው ዙር የምረቃ ሥነ-ስርዓት በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ተማሪዎች ተመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ዲን ተባባሪ ፕ/ር መብራቱ ለገሰ ካምፓሱ በጥቂት መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በመታገዝ በ2008 ዓ.ም 93 መደበኛ ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ስራ እንደጀመረ ጠቁመዋል።
ካምፓሱ ዛሬ ላይ በአንድ ጊዜ ከ5000 በላይ መደበኛ እና የተከታታይ ትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ላይ ደርሷል ሲሉም ዲኑ ተናግረዋል።
ተባባሪ ፕ/ር መብራቱ አክለውም፤ ካምፓሱ በዛሬው ዕለት በቅድመ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 330 ተማሪዎችን እንዲሁም 21 የክፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም መምህራንን ማስመረቁን አሳውቀዋል።
ለምሩቃን ባስተላለፉት መልዕክት በትምህርት ባሳለፉበት የህይወት መንገድ ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ ዋጋ የከፈለውን ውድ የሃገራቸውን ህዝብ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
በምረቃው ሥነ-ስርዓት የተገኙት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ለተመራቂዎች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ምሩቃን እና የምሩቃን ቤተሰብ ሁሉ የዓመታት ልፋታችሁን በማየታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ሀገራዊ አለመረጋጋት፣ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት እና ሌሎች መሰል ችግሮችን በመቋቋም ትምህርታችሁን አጠናቃችሁ በዛሬው ዕለት በመመረቃችሁ ይህን የምረቃ ሥነ-ስርዓት ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
በሌላ መልኩ፤ በሀገራችን ሰሜኑ ክፍል ተከስቶ የነበርው ጦርነት መላውን ሕዝብ ለብዙ እንግልት የዳረገበት ታሪክ አብቅቶ፥ ህርቀ ሰላም በሰፈነበት ማግስት ይህ ምረቃ ሥነ ስርዓት መካሄዱ የምረቃ ሥነ ስርዓቱን ልዩ እንዲሁም ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የዛሬ ምሩቃን በቀጣይ ጊዜያት የዩኒቨርሲቲው አልሙናይ በመሆን ቤተሰብነታቸው የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ከተመራቂዎች ጋር በመሆን ስራዎችን በቅርበት ይሰራል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ በመማር ማስተማር፣ በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ስርጸት እንዲሁም በመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ የተጀመሩ ተግባራት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተቀናጀ መልኩ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
በካምፓሱ የተጀመረው የትምህርት ልማት ስራን በማጠናከር ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ጥራትን መሠረት ያደረገ ሥራ እውን ይሆናል ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ ሠላማዊ መማር ማስተማርን በማዝለቅ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ብሎም ሕዝቡን በሙላት ለማገልግል ተግተን እንሰራለን ሲሉም ጠቁመዋል።
ተመራቂዎች በቀሪው የሕይወት ጉዟቸው መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቸው የተመኙት ፕሬዝዳንቱ፤ ምሩቃን በቀሪው የሕይወት ዘመናቸው መላ ሕዝቡን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዕጩ ዶ/ር ደስታ ደምሴ በበኩላቸው ትምህርት ትልቁ የሰው ልጅ ሀብት መሆኑን ገልጸው፤ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እና ዘላቂ ለውጥ ሁሉም በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በጎ ተጽህኖ የሚያመጣ ልዩነት ለመፍጠር ካስፈለገ ለትምህርት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተገቢ መሆኑን የተናገሩት የክብር እንግዳው፤ በትምህርት ልማት መስክ በካምፓሱ የተጀመረው ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ተቀናጅቶ መስራት ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል።
ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት እና ክዕሎት በመልካም ሥነ-ምግባር ታንጸው ስራ ላይ በማዋል ሕዝባቸውን በቅንነት እና በታማኝነት ለማገልግል መዘጋጀት እንዳለባቸው ዕጩ ዶ/ር ደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራርና አሉሙናይ ዳይሬክተር መ/ር ሳሙኤል ሳርካ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት በካምፓሱ በተካሄደው 4ኛ ዙር የምረቃ ሥነ ስርዓት በመደበኛ እና በተከታታይ የቅድመ ምርቃ የትምህርት እንዲሁም በከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም በአጠቃላይ 351 ተማሪዎች መመረቃቸውን አሳውቀዋል።
በካምፓሱ በተካሄደ የምረቃ ስነ-ስርዓት ትምህርታቸውን በሚገባ ያጠናቀቁ 330 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም 21 መምህራን በከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም የተመረቁ መሆናቸውን መ/ር ሳሙኤል አሳውቀዋል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ምሩቃን የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ተመራቂዎች ሙያዊ ቃለ-ምህላ በመፈፀም የምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ተጠናቋል።
በካምፓሱ በዛሬው ዕለት ከተመረቁ አጠቃላይ 351 ምሩቃን መካከል 224 ወንዶች ሲሆኑ፤ ቀሪ 127 ሴቶች ናቸው።
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት!!
➤ ጥር 06/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን