በዩኒቨርሲቲው በተካሄደ 11ኛ ዙር አመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍራንስ ተሳታፊዎች ግንባታው የተጠናቀቀውን «የሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል» ጎበኙ።
በዩኒቨርሲቲው በተካሄደ 11ኛ ዙር አመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍራንስ ተሳታፊዎች ግንባታው የተጠናቀቀውን «የሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል» ጎበኙ።
______________________________________________________________
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው 11ኛ ዙር አመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍራንስ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ተሳታፊዎች በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተገነባውን የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል ጎብኝተዋል።
ባለ ሰባት ሰንሰለታማ ተራራ በሆነው “ዳሞታ ተራራ” ግርጌ የሚገኘው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል አለም አቀፍ የጥራት መመዘኛ መስፈርትን በጠበቀ መልኩ የተገነባ መሆኑ ለጎብኚዎች ተብራርቷል።
ማዕከሉ ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች የሚሰጡትን ሙሉ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ትምህርት እና ስልጠና በመስጠት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ራዕይ በመሰነቅ የተመሰረተ መሆኑም ተመላክቷል።
ለጎብኝዎች በተደረገ ገለጻ ማዕከሉ 150 መኝታ ቤቶችን፥ የተለያየ መጠን ያላቸውን የተማሪ መማሪያ ክፍሎችን፣ መመገቢያ እና መሰብሰቢያ አዳራሾችን፣ ግብይት የሚሰጡ ሱቆችን፣ ማሳጅ ቤቶችን፣ ክሊኒክ፣ ላውንደሪ፣ ፕሌይ ስቴሽን እና ልዩ ልዩ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል በማስተማር እና በማሰልጠን ከማፍራት ባሻገር የማዕከሉ መቋቋም ለአካባቢው የቱሪዝም እድገት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጭምር ለጎብኚዎቹ ተብራርቷል።
ዩኒቨርሲቲው ከያዛቸው የትኩረት መስኮች አንዱ የቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ ልማት በመሆኑ የማዕከሉ መቋቋም በዘርፉ ከአጭር ጊዜ ስልጠና እስከ ፒ.ኤች.ዲ ደረጃ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጥ መሆኑም ተጠቁሟል።
ማዕከሉ ከትምህርትና ስልጠና ባሻገር በሆቴል ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች እኩል አገልግሎት የሚሰጥ እንዲሁም ማዕከሉ ያለበት አካባቢ ልዩ የመስዕብ ሥፍራ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑም ተመላክቷል።
ማዕከሉ ወደ ስራ ሲገባ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች ምቹ የስራ እድል እንደሚፈጥር፤ ለከተማው ዕድገት የራሱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እንዲሁም የውስጥ ገቢ አቅምን በማሳደግ ዩኒቨርሲቲው “ራስ ገዝ” ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑም ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ተገልጿል።
በወላይታ ሶዶ ከተማ ኮካቴ ማራ ጫሬ ቀበሌ የተገነባው ባለ አምስት ወለል (G+5) የሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል ሕንጻ ውስጣዊ ይዘት (ኢንቴርየር ዲዛይን) የወላይታን ብሔር ባሕላዊ ዕሴት በጠበቀ መልኩ የሚዋቀር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ማዕከሉ በቅርቡ ለሥራ የሚፈለጉ ቁሳቁሶችን በማሟላት አገልግሎት መስጠት የሚጀምር መሆኑ ለጎብኚዎች ተብራርቷል።
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት!!
➤ ግንቦት 05/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክWolaita Sodo University4/
ዌብሳይት፡ http://www.wsu.edu.et/
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን