በዩኒቨርሲቲው “አመክኗዊ ጥበብና የጥልቅ አስተሳሰብ ክህሎት ለሁለንተናዊ ማንነትና ለመልካም ስብዕና ግንባታ” በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ።
በዩኒቨርሲቲው “አመክኗዊ ጥበብና የጥልቅ አስተሳሰብ ክህሎት ለሁለንተናዊ ማንነትና ለመልካም ስብዕና ግንባታ” በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ።
በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ከወላይታ ዞን የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ መሆኑ ተመላክቷል።
___________________________________
በዩኒቨርሲቲው “አመክኗዊ ጥበብ እና የጥልቅ አስተሳሰብ ክህሎት ለሁለንተናዊ ማንነትና ለመልካም ስብዕና ግንባታ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለባለድርሻ አካላት ተሰጥቷል።
ስልጠናው በዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የስነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ክፍል ከምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ተባባሪ ዲን ረዳት ፕ/ር ሙሉቀን ታምራት፡ የሰውን ልጅ የሚገጥሙት ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች መንስኤ የጥልቅ አስተሳሰብ እና የአመክኗዊ ጥበብ ችግር መሆኑን የተለያዩ ተመራማሪዎች የጥናት ግኝት በመጥቀስ ተናግረዋል።
እንደ ሀገርም ሆነ በግል የሚያጋጥሙንን ማንኛውም ፈተናዎች እና ተግዳሮቶችን በጥልቅ አስተሳሰብ እና ሥነ-አመክኖ መፍታት እንዲቻል ስልጠናው ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ታሰቢ በማድረግ ለባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ መሆኑንም በንግገራቸው ገልጸዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በየተሰማሩበት የሥራ መስክ ከስልጠናው ባገኙት እውቀትና ክህሎት መነሻ ምክንያታዊ አስተሳሰብን እና ሥነ አመክኖን በመከተል ብሎም በጥልቀት በማሰብ ስራቸውን እንዲከውኑ ረዳት ፕ/ር ሙሉቀን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የሥነ-ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር እና የሥልጠናው ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት መምህር ጣሰው ታደሰ በበኩላቸው፡ በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ከወላይታ ዞን ከአስራ ስድስት የመንግስት መዋቅር የመጡ አመራሮች መሳተፋቸውን አሳውቀዋል።
የተቋም የሥራ ኃላፊዎችም ሆኑ ባለሙያዎች ለባለጉዳዮች አገልግሎት ሲሰጡ ከኢ-ፍትሀዊ አሰራርና ከወገንተኝነት ነጻ ሆነው፤ አመክኗዊ በሆነና በጥልቀት አስተሳሰብ ላይ ተመስርተው መሆን እንዳለበት ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን መምህር ጣሰው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ለሁሉም ዜጎች አስፈላጊ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልጸው፤ በሚቀጥሉት ግዜያት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በስፋት ለመስጠት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የታለመለትን አዎንታዊ ግብ ሊመታ የሚችለው ምክንያታዊ የሆኑ ዜጎች ተፈጥረው በየተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ በመርህ መስራት ሲጀመር እንደሆነ የተናገሩት አሰልጣኝ መምህር ማቱሳላ ሱንዳዶ ናቸው።
ለዚህም የአመክኗዊ ጥበብንና የጥልቅ ስተሳሰብን ክህሎት በሰልጣኞች ዘንድ ማስረጽ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ባላው አግባብ በትብብር መስራትን ይጠይቃል ሲሉም አሰልጣኙ ጠቁመዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች የትኛውንም ውሳኔ ሲሰጡ ምክንያታዊ በሆነ መንገድና በጥልቀት በማሰብ የመልካም ስብዕና ግንባት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡