በዩኒቨርሲቲው የሁነት አስተዳደርና የብሔር ብሄረሰቦች የባህል ማስተዋወቂያ መድረክ ተካሂዷል
በዩኒቨርሲቲው የሁነት አስተዳደርና የብሔር ብሄረሰቦች የባህል ማስተዋወቂያ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎች የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።
___________________________________
ትምህርታቸውን በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል እየተከታተሉ ያሉ የቅድመ ምረቃ መደበኛ ተመራቂ ተማሪዎች መድረኩ እንደተዘጋጀ የኮሌጁ አስተዳደር አሳውቋል።
በሁነት ዝግጅትና አስተዳደር /Event Management እንዲሁም በብሔር ብሄረሰቦችን ባህል ማስተዋወቅ ላይ በማተኮር በተዘጋጀው መድረክ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የኮሌጁ መምህራን ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚክ ጉዳዩች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ዴአ ዩኒቨርሲቲው ከመቼውም ጊዜ በላይ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አሳውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለተግባር ተኮር ትምህርት አጽንኦት በመስጠት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር እና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ተልዕኮ እና ለይቶ በሚሰራቸው የትኩረት መስኮች መሠረት የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርስቲ መሆኑን ዶ/ር ሙላቱ ገልጸው፤ በንድፈ ሀሳብ የሚሰጡ የትምህርት መርሃ ግብሮች በተግባር ልምምድ የተደገፉና የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አሳውቀዋል።
ተማሪዎቻችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማገናኘት እና ልምድ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ማበረታታት አስፈላጊ እና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የተዘጋጀው የሁነት ዝግጅትና አስተዳደር እንዲሁም የብሔር ብሄረሰቦች ባህል የማስተዋወቂያ መድረክ በሥርዓተ-ትምህርት መሠረት በተግባር ለመተርጎም የተሠራውን ሥራ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሌጁ ለተግባራዊ ሥርዓተ ትምህርት መረጋገጥ እያደረገ ያለው ትጋት የሚደነቅ መሆኑን እና ሌሎችም ይህን ፈለግ መከተል እንዳለባቸው ዶ/ር ሙላቱ ጠቁመው፤ ኮሌጁ የበለጠ እንዲተጋ ተገቢው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደምቀጥል አሳውቀዋል።
የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን የሆኑ ረዳት ፕሮፌሰር ዘገዬ ጳውሎስ በበኩላቸው ኮሌጁ በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ከ4500 በላይ መደበኛ እና የሳምንት መጨረሻ ተማሪዎችን እንዲሁም ከ200 በላይ የሚሆኑ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን በ6 የትምህርት ፕሮግራሞች ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።
በመድረኩ የማርኬቲንግ ትምህርት ክፍል ተመራቂ በሆኑ ተማሪዎች በሥርዓተ ትምህርታቸው (Curriculum) መሠረት የተማሩትን ትምህርት በተግባር ለማሳየት የሠሩት ሥራ አበረታች መሆኑን ዲኑ ገልጸዋል።
ምሩቃን ተማሪዎቹ ይህን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ሌሎች የትምህርት ክፍሎችም ይህንን ልምድና ተሞክሮ እንደ ትምህርት በመውሰድ ለተግባራዊነቱ መትጋት እንዳለባቸው ረዳት ፕ/ር ዘገየ አሳስበዋል።
ለመድረኩ ስኬታማነት ተመራቂ ተማሪዎቹ የድጋፍ ደብዳቤ በመያዝ በወላይታ ዞን እንዲሁም በሶዶ ከተማ ውስጥ ያሉ ተቋማትን፣ ድርጅቶችንና ታዋቂ ግለሰቦች የሀሳብ፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ መጠየቃቸውን ዲኑ አሳውቀው፤ ምሩቃን ተማሪዎቹ ከተመረቁ በኃላ የሥራ አለም እና ኢንዱስትሪዎች በቀላሉ መቀላቀል እንዲችሉ ልምድና ተሞክሮ ማግኘታቸውን የሚያሳይ አኩሪ ተግባር መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
የኮሌጁ ዲን አክለውም፤ ለምሩቃን ተማሪዎቹ ተገቢውን ትብብር ላደረጉ ተቋማት/ድርጅቶች እና ግለሰቦች ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸው፤ በተለይም ለወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላደረጉት ድጋፍና ትብብር በኮሌጁና በማርኬቲንግ ትምህርት ክፍል ስም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በኮሌጁ የማርኬቲንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት መ/ር ለገሰ ለማ በበኩላቸው ጠቀሜታ ያላቸው መሰል ተግባር ተኮር ሥራዎች በሥርዓተ-ትምህርት መነሻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት!!
➤ ጥር 07/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት
ዌብሳይት፡ http://www.wsu.edu.et/
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን