በዩኒቨርሲቲው 11ኛው አመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ተካሄደ።
በዩኒቨርሲቲው 11ኛው አመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ተካሄደ። (ግንቦት 04/2015 ዓ.ም)
“ተግባራዊ ምርምር፣ ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል 11ኛው አመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
______________________________________________
በመድረኩ በመገኘት ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መስፍን ቢቢሶ፡ በተያዘው በጀት ዓመት ዘርፉ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት 153 የምርምር፣ 63 የማህበረሰብ አገልግሎትና ተሳትፎ እንዲሁም 7 የቴክኖሎጂ ሽግግር ፕሮጀክቶችን አከናውኗል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ላለፉት አራት ዓመታት በስኮፕስ፥ በዌብ ኦፍ ሳይንስና ፓብሜድ በተሰኙ ዓለም አቀፍ እውቅና ባለቸው ጆርናሎች ከ800 በላይ ጥናታዊ የምርምር ጽሑፎችን አሳትመዋል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በተያዘው የትምህርት ዘመን 176 የጥናትና ምርምር ጽሑፎች በታዋቂ ጆርናል መታተሙንም ጠቁመዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን አክለውም፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ተግባራዊ ከተደረጉ 63 የማህበረሰብ ተሳትፎ ፕሮጀክቶች በትንሹ 250,000 ያህል የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረው፤ ከ100 በላይ ከሚሆኑ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ተቋማት ጋር አጋርነትና ትብብር በመመስረት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
እውቀትን፥ ችሎታንና ክዕሎትን በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ምሁራን፣ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች መካከል ማካፈል፤ ለዘላቂ የልማት ግቦች እውን መሆን የሚጠቅሙ የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ማሰራጨት እንዲሁም ለልማት ፖሊሲ ፋይዳ ያላቸውን ምክረ ሀሳቦችን መስጠት የኮንፍረንሱ ዋና ዋና ግቦች እንደሆኑም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።
ሀገራዊ የልማት ግቦችን በተገቢው ማሳካት እንዲቻል ተግባራዊ ምርምርን፣ ፈጠራን እና ቴክኖሎጂን ለዘላቂ ልማት በሚውል አግባብ በማስተሳሰር ዩኒቨርሲቲው የተቻለውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑንም ፕሮፌሰር መስፍን ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በንግግራቸው፡ ዩኒቨርሲቲው ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርትና ስልጠና በመስጠት፣ እውቀትና ቴክኖሎጂን በመፍጠር እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር ትስስር በመፍጠር በሀገር፣ በአካባቢ እና በተቋም ደረጃ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት እንዲረጋገጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያካሄድ ቆይቷል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ሁሉን አካታች የሆነ የሳይንስ ጆርናል በማቋቋም ችግር ፈቺና ልማታዊ የጥናት ውጤቶች ህትመት ተደረሽነት ላይ በስፋት መስራቱ፤ የትኩረት መስኮችን በመለየት የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በስፋት ተደራሽ መሆኑ፤ ለዘርፉ መንግስት ከሚመድበው ውስን ሀብት በተጨማሪ ከአጋሮች ጋር በመተባበር በዘርፉ ሰፊ ስራ መሰራቱ፤ ምርምርን ለማቀላጠፍ እና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለመስጠት የምርምር ማዕከላት መስፋፋቱ እንዲሁም የምርምር ባህልን በአቻ ግምገማ ከማሻሻል ረገድ የተከናወኑ ጉልህ ተግባራት እንደሆኑ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአካዳሚክ ስራው ላይ መምህራንን፣ ተማሪዎችን እንዲሁም የባለድርሻና የአጋር አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር አግባብነት እና ጥራት ያለው ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈጥር መቆየቱን ፕሮፌሰር ታከለ አሳውቀዋል።
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር የማድረግ ልምድና ባህል ያለው ተቋም መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ኮንፈረንስ በማዘጋጀት ሳይንሳዊ እውቀቶችን የማፍለቅ እና የማሰራጨት ተግባር ላይ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
ምሁራን የምርምር ግኝቶቻቸውን በመድረኩ እንዲያስተዋውቁና ተማሪዎችም በወቅታዊ ሳይንሳዊ ውይይትና ክርክር ታድመው እውቀት፣ ክዕሎትና ልምድ እንዲያገኙ ኮንፈረንሱ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ፕሮፌሰር ታከለ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች ከመማር ማስተማር ተግባራቸው በተጨማሪ አግባብነት ባለው ችግር ፈቺ የምርምር፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ የሚጠበቅባቸውን ምሁራዊ ሚና እንዲወጡ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።
በተያዘው የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው 130 ሳይንሳዊ ጥናቶችን እንዲሁም 50 የማህበረሰብ ተሳትፎ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ፕሮጀክቶችን እንዲተገበሩ ድጋፍ ማድረጉን ፕሮፌሰር ታከለ አሳውቀው፤ ምሁራን የመጨረሻ የምርምር ውጤቶች ለዋና ተጠቃሚዎች በሚጠቅሙ መንገዶች እንዲሰራጩ በኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በጉባኤው የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር የማነህ ብርሃን ጥናትና ምርምር ስራን በተመለከተ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ በማተኮር ሠፊ ገለጻ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኮንፍራንሱ በዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የምርምር፣ ማኅበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች አፈፃፀም ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት ዶ/ር እዮብ እሸቱ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
ከተመራማሪዎች በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የPhD ተማሪዎች፣ ከወላይታ ዞንና የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ 135 የማኅበረሰቡ ተወካዮች፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ጥሪ እንግዶች በአውደ ምክክሩ ተሳትፈዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ኮንፍራንስ ከ18 የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ምርምር ማዕከላት የመጡ ተመራማሪዎች 36 ያህል የጥናትና ምርምር ውጤቶች እንደሚያቀርቡ እንዲሁም የቴክኖሎጂ እና የፖስተር ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት!!
➤ ግንቦት 04/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክWolaita Sodo University4/
ዌብሳይት፡ http://www.wsu.edu.et/
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን