የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ያስገነባውን ባለ 5 ወለል ሕንጻ (G+5) የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ለመምህራን ርክክብ አደረገ
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ያስገነባውን ባለ 5 ወለል ሕንጻ (G+5) የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ለመምህራን ርክክብ አደረገ።
___________________________________
በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ለሚሰሩ መምህራን መኖርያ ቤት አገልግሎት እንዲውል የተገነባ ባለ 5 ወለል ሕንጻ (G+5) የጋራ መኖርያ ቤት ግንባታው ተጠናቆ ለመምህራን ርክክብ ተደርጓል።
ሕንጻው ከ 54 ሚሊየን ብር በሚበልጥ በጀት የተገነባ መሆኑን እና 24 መምህራንን ከሙሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲችል ተደርጎ አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላለት መሆኑ በቁልፍ ርክክብ ሥነ-ስርዓት ላይ ተመላክቷል።
በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ ዩኒቨርሲቲው በመምህራን ልማት ላይ በማተኮር መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለመምህራን ምቹ የሥራ ከባቢያዊ ሁኔታን በመፍጠር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በተቀናጀ መልኩ መትጋት ተገቢ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
የልማትና የእድገት አንቀሳቃሽ ሞተር የሆኑት መምህራን ለስራቸው አመቺና አስፈላጊው መሰረተ ልማት ሊሟላላቸው ይገባል ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ እንደ ተቋም በመምህራን ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አሳውቀዋል።
በቀጣይም በመምህራን የጋራ መኖርያ ቤት ግንባታ፣ በነጻ ህክምና እና በነጻ ትምህርት እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት አበክረን በተቀናጀ አግባብ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ።
ከመምህራን የጋራ መኖሪያ አቅርቦትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ከዚህ ቀደም 4 ባለ አምስት ፎቅ (G+5) ዘመናዊ የመኖርያ ህንጻዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ለመምህራን ርክክብ መደረጉን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ለሚሰሩ መምህራን የተገነባው ይህ እጅግ ዘመናዊ (G+5) ሕንጻ አምስተኛው መሆኑንም ፕ/ር ታከለ ታደሰ አመላክተዋል።
የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ማመቻቸት፣ ምቹ እንዲሁም ሠላማዊ የሥራ ሁኔታን መፍጠር ለመምህራን ከፍተኛ ፋይዳ ከመስጠቱ ባሻገር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ሲሉም ፕ/ር ታከለ ተናግረዋል።
በነጻ ትምህርት ዕድል፣ በነጻ ሕክምና እንዲሁም ከአዋሽ ባንክ ጋር በተገባው ውል መሰረት መምህራን ቤት እና ተሽከርካሪ እንዲገዙ ብድር የማመቻቸት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ጠቁመዋል።
የሕንጻው ግንባታ በተገቢው ተጠናቆ ለርክክብ እንዲበቃ ላደረጉ አካላት በተለይም ለሕንጻው የግንባታ ኮንትራክተር እና አማካሪ አካላት ፕሬዝዳንቱ ምስጋና ይገባቸውል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ተክሌ ሌዛ በበቡላቸው ከ 54 ሚሊየን ብር በሚበልጥ በጀት የተገነባው ባለ 5 ወለል( G+5) የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታው ተጠናቆ ለመምህራን የቁልፍ ርክክብ መደረጉን አሳውቀዋል።
በዩኒቨርሲቲው ካፒታል በጀት የተገነባው ይህ ዘመናዊ ህንጻ 24 መምህራንን መያዝ የሚችል መሆኑን እንዲሁም አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ያካተተ ህንጻ መሆኑን ጭምር ዶ/ር ተክሌ ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ርክክብ የተደረገላቸው መምህራን የሕንጻውን ደህንነት ሊጠብቁ እንደሚገባ እንዲሁም የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ቦሻ በጋራ መኖሪያ ቤት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ያወጣውን መመሪያ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም በዩኒቨርሲቲው ለጋራ መኖሪያ ቤት አስተዳደር አገልግሎት እንዲውል ለወጣው መመሪያው ተፈጻሚነት ሁሉም ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት በማለት አሳስበዋል።
የዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ዲን የሆኑት ተባባሪ ፕ/ር መብራቱ ለገሰ በበኩላቸው የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ተጠናቆ ለመምህራን እንዲተላለፍ በመደረጉ ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅማንት ምስጋና አቅርበዋል።
አሁን ላይ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ 4 ያህል ባለ አምስት ወለል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው ሲጠናቀቅ የመምህራን መኖርያ ቤት አቅርቦት ተደራሽነት 90% እንደሚሆን ከግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት!!
➤ ጥር 07/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት
ዌብሳይት፡ http://www.wsu.edu.et/
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን