የዩንቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል የ2015 አጋማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ።
የዩንቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል የ2015 አጋማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ።
___________________________________
የወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ አስተዳደር ካውንስል በ2015 አጋማሽ ዓመት በየዘርፉ የተከናወኑ ቁልፍ ተግባራትን ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማድመጥ ግምገማ አካሂዷል።
በዩኒቨርሲቲው በተካሄደ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በ2015 አጋማሽ አመት በፕሬዝዳንት፣ በአካዳሚክ ጉዳዮች፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት፣ በአስተዳደር እና ተማሪዎች አገልግሎት እንዲሁም በቢዝነስና ልማት ዘርፎች የተከናወኑ ቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ባለፉት ስድስት ወራት በየዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ከግለሰብ ፈጻሚ እስከ ዘርፍ መዋቅር ባሉ አደረጃጀቶች የተገመገመ መሆኑን አሳውቀዋል።
በየዘርፉ ባሉ መዋቅራዊ አደረጃጀቶች በተካሄደ የተናጠል አፈጻጸም ግምገማ ወቅት ነጥረው የወጡ ተግባራትን በተሞክሮነት አስፍቶ ለማስቀጠል እንዲሁም በሂደቱ ለተስተዋሉ ውስንነቶችም የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም ይህ የግምገማ መድረክ መዘጋጀቱን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ለተቋም ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲሁም ቀጣይነት ላለው የዕድገት ጉዞ በመማር ማስተማር፣ በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር፣ በአሳታፊ ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግርና ስርጸት መስክ የተጀመሩ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተቀናጀ መልኩ መስራት ተገቢ መሆኑንም ፕሮፌሰር ታከለ አመላክተዋል።
እንደ ተቋም ብልሹ አሠራርን እና ሌብነትን መታገል፤ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጣን ምላሽ መስጠት፤ ታቅደው የሚፈጸሙ ተግባራት በተገቢው መደገፍ፥ መከታተል እና አመራር መስጠት በየዘርፉና በየደረጃው ካሉ አመራሮች ይጠበቃል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ከማረጋገጥ እና ከማዝለቅ፤ የትኩረትና የልህቀት ማዕከልን መሰረት በማድረግ የትምህርት ፕሮግራሞችን ከመተግበር፤ በምርምር ላይ የተመረኮዘ የማህበረሰብ አገልግሎት ከመስጠት፤ ከምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር ከመፍጠር፤ የጆርናል አክሬዲቴሽን እና ህትመትን በውጤታማነት ከመተግበር፤ ተቋማዊ የዲጂታላይዜሽን ተግባራትን ከማጠናከር፤ የመሠረተ-ልማትና ግንባታ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ከማሻሻል እንዲሁም የሃብት አስተዳደርና ተጠያቂነትን ከማስፈን ረገድ ባለፉት ስድስት ወራት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ፕሮፌሰር ታከለ አሳውቀዋል።
በመጪው ሀምሌ ወር በሁሉም የትምህርት መስኮች እና መርሀግብሮች ለሚተገበረው የመውጫ ፈተና ትግበራ የተጀመሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የበለጠ ማጠናከር እና ተማሪዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ፤ አዲሱን መዋቅራዊ አደረጃጀት በተገቢው መተግበር አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር ችግሮችና ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ መስጠት በቀጣይ ጊዜያት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል ባለፉት ስድስት ወራት በየዘርፉ የተከናወኑ የቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያስተላለፈ ሲሆን: በዋናነትም ለትምህርት ጥራት መሻሻል በቅንጅት መስራት፤ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፤ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን ማጠናከርና ማዘመን፤ ታቅደው የተፈጸሙ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን ለስርፀት ማዘጋጀት፤ የማህበረሰብ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎን ማጠናከር እንዲሁም አስተዳደራዊ የድጋፍ እና ክትትል ሥራን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ ተመላክቷል።
በተጨማሪም የልማትና የፕሮጀክት ትግበራ አፈጻጸምን ማሻሻል፤ አደረጃጀቶችን እና አሰራሮችን ማጠናከርና ማዘመን፤ የተቋሙን ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎና ግንኙነት ማጠናከር፤ ነባር አሰራሮችን ማሻሻል እና አዳዲስ አሰራሮችን ማፍለቅ፥ ማስተዋወቅ እና የትግበራ ደረጃን ማሻሻል እንዲሁም የዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በሁሉም ተግባራት በማካተት ተፈጻሚነቱን መከታተልና መደገፍ በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲተገበሩ አስተዳደር ካውንስሉ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ማህበርና የተማሪዎች ሕብረት የቀጣይ ስድስት ወራት የሥራ ዕቅድ የቀረበ ሲሆን፤ በቀረቡ የአፈጻጸም ሪፖርቶችና ቀጣይ የሥራ እቅዶች ላይ ከአስተዳደር ካውንስል ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ምላሽና ማብራርያ ተሰጥቷል።