ዩኒቨርሲቲው ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በ8 ሚሊየን ብር የሚተገበር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመ።
ዩኒቨርሲቲው ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በ8 ሚሊየን ብር የሚተገበር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመ።
ፕሮጀክቱ የተፈናቀሉ ማህበረሰቦችን መልሶ በቋቋም እና በማበረታታት የተቀናጀ ኑሮ እንዲመሩ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።
በወላይታ ዞን በአራት ጣቢያዎች ሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት ለ 488 ግለሰቦች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የመጡ ልዑካን ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል።
ልዑካን አባላቱ በፕሮጀክቱ አተገባበር ላይ እና ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይ በመምከር ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ተቋሙ ከመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ረገድ በተቀናጀ አግባብ እየሰራ መቆየቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ በመድረኩ አሳውቀዋል።
የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ለማሕበረሰብ ዘላቂ ተጠቃሚነት መትጋት ከሁሉም ይጠበቃል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም ፕሮጀክት የታለመለትን ግብ እንዲመታ ተገቢው ድጋፋዊ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
ከአደጋ ሥጋት ነጻ የሆነና ለአደጋ የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን የጋራ ጥረት በዕውቀት መምራት ያስፈልጋል ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ ለዚሁ ምሁራን የድርሻቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት መ/ር ብርሃኑ ሌንጫ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፤ ሁለቱ ተቋማት ተፈናቃዮች ላይ በማተኮር የጋራ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት የሚያካሄዱ መሆኑን አብራርተዋል።
በሁለትዮሽ የትብብር ማዕቀፍ ተፈናቃዮችን በተቀናጀ መልኩ መልሶ ለማቋቋም እና ኑሯቸውን ለመደገፍ ያስችል ዘንድ ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ ለሁለት ዓመታት የሚተገበር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለፕሮጀክቱ ትግበራ 8 ሚሊየን ብር መመደቡን ያሳወቁት አስተባባሪው፤ በጠቅላላው 488 ግለሰቦች በፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው አመላክተዋል።
ከአጠቀላይ ተጠቃሚዎች 192 ያህሉ በቀጥታ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሆኑ እና ቀሪ 296 ያህሉ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመጠቆም።
ፕሮጀክቱ በወላይታ ዞን በአራት ጣቢያዎች በዋናነትም በሶዶ ከተማ፣ በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ሶሬ ሀምባ ቀበሌ፣ በአረካ 01 እና በአረካ 02 እንደሚተገበር መ/ር ብርሃኑ በገለጻቸው አሳውቀዋል።
በመድረኩ የተገኙት የምርምርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ልቢቢሶ እንደ ተቋም ማሕበረሰቡን ከአደጋ ስጋት መታደግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በትብብር የተጀመረው የሁለትዮሽ የትብብር ማዕቀፍ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት መስክ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።
ወላይታ እና አካባቢው ከፍተኛ የመሬት ጥበት እና የሕዝብ ጥግግት ያለበት በመሆኑ ለአደጋ እጅግ ተጋላጭ ነው ያሉት ደግሞ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት
ዶ/ር ሙላቱ ዴአ ናቸው።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ የሕብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ መለወጥ እንዲቻል በችግሩ ልክ ተገቢው ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
የተፈናቃዮችን የምግብ ዋስት በማረጋገጥ ዘላቂ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ተገቢው ድጋፍና ክትትል ሊደረግ ይገባል ሲሉ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም ቦሻ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮችን ማዕከል በማድረግ በሁለት ምዕራፍ ለ 2 ዓመታት የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፤ የተረጋጋ እና ከአደጋ ሥጋት
ነጻ የሆነ ማሕብረሰብን መገንባት በሚያስችል መልኩ ይተገበራል ተብሏል።
ተቋማቱ ዘላቂ አጋርነትና ትብብር በማጎልበት ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመተግበር ዕቅድ በመያዝ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት!!
➤ ጥር 08/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት
ዌብሳይት፡ http://www.wsu.edu.et/
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን