ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
_______
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ የ2015 ዓ.ም የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ለመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድህነት ሲል መከራና ስቃይን ለተቀበለበት እና ሞትን ድል አድርጎ ለተነሳበት የትንሳኤ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ፕሬዝዳንቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ገልጸዋል።
“ስቅለቱ እና ትንሳኤው” ፍቅርን፣ ይቅርታን እና በፅናት ማሸነፍን ያስተምራል ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ ክርስቶስ በስቅለቱና በትንሳኤው ካሳየን በጎነት፥ ፍቅርና ርህራሄ አልፎም ድል አድራጊነት በመማር “ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን፣ መሰጠትና ፍፁማዊ ደግነትን ልናሳይ ይገባል” ብለዋል።
የክርስትና አስተምህሮት እንደሚያስረዳን “ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ህይወቱን የሰጠው ስለ ሰው ልጅ ፍፁም ፍቅር ነዉ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ እኛም ይህን አርዓያነት በመከተል በፍጹም ፍቅር እንድንኖር እና መስጠትን የህይወታችን አካል ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
የትንሳኤ በዓል “ከፈተና ማዶ አስገራሚ የድል አድራጊነት ብስራት መኖሩን የሚያውጅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የሰው ልጅ በማንኛውም ምድራዊ ፈተና መካከል ቢሆን እንኳ ነገ ትልቅ ተስፋ መኖሩን እንዳይዘነጋ የሚያመላክት የእውነት መሰረት መሆኑንም ጠቁመዋል።
እርስ በርስ በክፋትና በተንኮል ከመጠማመድ ተለይተን፣ የተንኮል አስተሳሰብን ቀብረን በምትኩ የትህትና፣ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት እንዲሁም የአንድነት በጎ አስተሳሰብ እንድናጎለብት ጽኑ መሠረት የሚጥል ኃይማኖታዊ ክብረ በዓል እንደሆነም ስለ ትንሳኤ በዓል ፕ/ር ታከለ አብራርተዋል።
እንደ እምነቱ አስተምህሮ “ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው ዋጋ የይቅርታ ህይወትን ተምረን በይቅርታ ልንሻገር ይገባል” ሲሉ የተናገሩት ፕ/ር ታከለ፤ በዓሉ የይቅርታና የፍቅር ምልክት መሆኑን በመገንዘብ፥ በዓሉን ስናስብ የበደሉንን ይቅር በማለት፣ ዕርቅ በማድረግና ሠላም በማውረድ በፍጹም ፍቅር በመመላለስ ሊሆን ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
የተወለደው እንዲያድግ፣ ወጣት አገር እንዲረከብ፣ ጎልማሳው ለአገሩ በርትቶ እንዲሰራ፣ አረጋውያን በክብር እንዲጦሩ የሚያስፈልገው እርቅ፣ ሰላምና ፍቅር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ቂም እና ጥላቻን በይቅርታ በማለፍ የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ተቋም በሚያጋጥሙን ጊዜያዊ ፈተናዎች ሳንሸበር፣ ለዘላቂ ህዝባዊ ጥቅም መረጋገጥ ተግተን መስራትና መጓዝ ይጠበቅብናል ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ የክርስቶስን አርዓያነት በመከተልና እውነት ላይ በመቆም እንዲሁም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም በፍቅር እንድንኖር እና መስጠትን የህይወታችን አካል ልናደርግ ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።
የዘንድሮውን የትንሳዔ በዓል ስናከብር እንደ ሀገርም ሆነ፥ እንደ ተቋም ባላፉት ጥቂት የለውጥ አመታት የታዩ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን በመውሰድ፤ በቀጣይ ጊዜያት አዲስ ነገር በምንሰራበት ሁኔታ ላይ በማተኮር መሆን አለበት ያሉት ፕ/ር ታከለ ፤ በሚቀጥሉት ጊዜያትም ለሚያጋጥሙን ፈታኝ ሁኔታዎች እጅ ሳንሰጥ ለውጤታማነት የበለጠ ተቀናጅተን በትብብር ልንሰራ ይገባል በማለት ተናግረዋል።
ትንሳኤን ስናስብ ከችግር በኋላ ደስታ፤ ከሞት በኋላ ትንሳኤ፤ ከጨለማ በኋላ ብርሃን መኖሩን በማስታወስ መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላትም ከመቼውም ጊዜ በላይ በመግባባት፣ በመደማመጥ እና አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር በሁሉም መስኮች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ የዘወትር ድጋፍ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመቀጠልም ዩኒቨርሲቲያችን በመማር ማስተማር፣ በችግር ፈቺ ጥናት እና ምርምር፣ በአሳታፊ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ስርጸት እንዲሁም በሌሎች አስተዳደራዊና ልማታዊ መስኮች የጀመራቸውን የልማት ስራዎች ከዳር በማድረስ ለተቋማችን ራዕይ መሳካት በትብብር መስራት ተገቢ እንደሆነም ፕ/ር ታከለ አሳስበዋል።
የትንሳኤን በዓል ስናከብር በተለመደው የመተጋገዝና የአብሮነት መንፈስ ሆነን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ እና ለአደጋ የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በላቀ ተነሳሽነት በመርዳት፥ አረጋዊያንን በመደገፍ፣ የወደቁትን በማንሳት፣ የታረዙትን በማልበስ እና የተራቡትን በመመገብ እንዲሁም ያላችሁ ለሌላቸው በማካፈል የተለመደው በጎ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ባስተላለፉት መልዕክት።
በድጋሚ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሠላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት እንዲሆን ፕሬዝዳንቱ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዕውቀትን በተግባር!!