ከአየርላንድ “ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዱብሊን” ለትምህርታዊ ጉብኝት ለመጡ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።
ከአየርላንድ “ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዱብሊን” ለትምህርታዊ ጉብኝት ለመጡ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ከአየርላንድ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዱብሊን ለይፋዊ ትምህርታዊ ጉብኝት ለመጡ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል አደረገ።
____________________________________
በሀገረ አየርላንድ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዱብሊን(UCD) ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ዓመታትን ያስቆጠረና በሁለትዮሽ የጋራ ትብብር ማዕቀፍ ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት አላቸው።
ሁለቱ ተቋማት በBRTE ፕሮጀክት ላይ ባላቸው ስምምነት መሰረት በተማሪዎች እና ሰራተኞች ልውውጥ፣ በልምድ ልውውጥና ተሞክሮ ሽግግር፣ በአጭርና በረዥም ጊዜ ስልጠና፣ በጋራ በሚተገበሩ ስርዓተ ትምህርቶች ቀረጻ እና በድህረ ምረቃ የትምህርት ዕድል፣ በጋራ በሚተገበሩ የምርምር ፕሮጀክቶች እና መሰል ተግባራት ላይ በአጋርነትና የትብብር ማዕቀፍ በስፋት ሲሰሩ ቆይተዋል።
በተማሪዎች እና ሰራተኞች ልውውጥ ረገድ ተቋማቱ ልምድ እና ተሞክሯቸውን የተጋሩበት ሰፊ ዕድል በፕሮጀክቱ የተፈጠረ ሲሆን፤ 12 ያህል የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህራንም በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዱብሊን በተለያዩ የትምህርት መስኮች የፒ.ኤች.ዲ ትምህርት ዕድል አግኝተዋል።
በዛሬው ዕለትም የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ከአየርላንድ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዱብሊን ለይፋዊ ትምህርታዊ ጉብኝት ለመጡ የተማሪዎች ልዑክ አባላት ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል።
በአቀባበል መድረኩ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ የሰው ዘር መገኛና ጥንታዊት ታሪካዊ ሀገር ስለሆነችው ኢትዮጵያ እንዲሁም «ዕውቀትን በተግባር» በሚል መሪ ቃል ስለሚታወቀው እና አረንጓዴ፣ ጽዱ፣ ሰላምዊና ሕብረብሔራዊ ተቋም ስለሆነው ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ገለፃ አድርገዋል።
በዩሲዲ የፕሮጀክቱ ዋና ኃላፊ ፕሮፌሰር ፓት፡ በፕሮጀክቱ የመጨረሻ አምስት ዓመታት ውስጥ ስለተመዘገቡ ቁልፍ ስኬቶች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፤ የተማሪዎቹ ይፋዊ ትምህርታዊ ጉብኝት ሁለቱ ተቋማት በተማሪዎች ልውውጥ ረገድ በቀጣይ የሚያስጀምሩት የሁለተኛ ዙር ፕሮጀክት የልምድ ልውውጥ አካል በመሆን ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
ለአስር ቀናት ለሚቆይ ይፋዊ ትምህርታዊ ጉብኝት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጡት እነዚህ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዱብሊን በሂዩማኒቴርያን አክሽን/MSc in Humanitarian Action/የትምህርት መስክ የማስተርስ ተማሪዎች መሆናቸው በመድረኩ ተጠቁሟል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የBRTE ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ኩማ በበኩላቸው፡ ተማሪዎቹ በቆይታቸው ከወላይታ ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ጋር በመተዋወቅ የሰብአዊ ተግባር ፖሊሲዎችን እና መርሃ ግብሮችን ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች እና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር በማስተሳሰር ግንዛቤ እንዲያገኙ የትምህርታዊ ጉብኝቱ መርሃ ግብር አስቻይ መሆኑን ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በቆይታቸው የወላይታን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ተቋማት የሚጎበኙ መሆኑ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፤ ትምህርታዊ ጉብኝቱ የግብረ ሰናይ ስራዎች እና ፖሊሲዎች እንዴት የማህበረሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መቀረፅ እንዳለባቸው ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ አላማውን ያደረገ እንደሆነ ተመላክቷል።
የትምህርታዊ ጉብኝቱ ልዑካን አባላት በማኔጅመንቱ ከተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በኋላ በዋናው ግቢ የተገነባውን የወላይታ ባህል ሙዚየምን ጨምሮ የተለያዩ ልማታዊ ስራዎችን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት!!
➤ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክWolaita Sodo University4/
ዌብሳይት፡ http://www.wsu.edu.et/
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን